ሚኒስቴሩ ከዲፒ ወርልድ ጋር በበርበራ ኮሪዶር ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ዲፒ ወርልድ

ሚያዝያ 28/2013 (ዋልታ) – የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ዲፒ ወርልድ የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ዘርፍ ውጤታማነት ለማሳደግ እና የበርበራ ኮሪደርን ለማልማት የሚያስችል የስትራቴጂያዊ አጋርነት መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ እና በዲፒ ወርልድ ቡድን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሱልጣን አህመድ ቢን ሱሌይማን የፈረሙት ስምምነቱ የሀገሪቱን የሎጀስቲክስ ልማት ለማሳደግ በአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ በተመላከተው እና በብሔራዊ ሎጂስቲክስ ፖሊሲና ሎጂስቲክስ ስትራቴጂው በተቀመጠው አማራጭ የሎጂስቲክስ ኮሪደሮችን የማስፋት ዕቅድን ተከትሎ ነው ተብሏል።

በዚህም በኮሪደሩ የኢትዮጵያ ወገን የሎጂስቲክስ ውጤታማትን የሚያረጋግጡ እንደ መዳረሻ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣ ደረቅ ወደብ፣ የቀዝቃዛ ጭነት ሎጂስቲክስ፣ የእህል ማከማቻዎች የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶችን የመገንባት እንዲሁም በዘመናዊ ቴክሎኖሎጂ የተደገፈ የሎጂስቲክስ ሥርዓት መዘርጋትን ያካተቱ ሥራዎችን እንደሚከናወኑ ተገልጿል፡፡

ይህም ሃገሪቱ ያለባትን የሎጂስቲክስ ሥርዓት ውጤታማነት ችግር በሰፊው እንደሚቀርፍ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞዋን ስትጀምር አበረታች የልማት አቅም መፍጠር እንዲሁም የሎጀስቲክስ ኢንዱስትሪውን መለወጥ አስፈላጊ በመሆኑ በሴክተሩ በፖሊሲ እና ስትራቴጂ የተደገፉ የሚጨበጡ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ዲፒ ወርልድ በኢትዮጵያ የበርበራ የሎጂስቲክስ ኮሪደርን ለማልማትና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ እንዲሁም የኮሪደር ትራንስፖርት መሠረተ ልማቱን ለማከናወን እስከ 1 ቢሊየን ዶላር መዋዕለ ንዋይ እንደሚያውል ይጠበቃል፡፡