ሚኒስቴሩ ከ213 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 6 ስምምነቶችን ተፈራረመ

ሚያዝያ 14/2014 (ዋልታ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ213 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ስድስት ስምምነቶችን ተፈራርሟል፡፡

ከስምምነቶቹ ውስጥ ከ41 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን እያስተናገዱ ላሉትና በዚህ ሳቢያ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አቅርቦት ላይ ተግዳሮት ለገጠማቸው የጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሃን እና ሰመራ- ሎጊያ ከተሞች የሚውል ነው ተብሏል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደተገለጸው፣ ከስድስቱ ስምምነቶች ሁለቱ ለአራቱ ከተሞች 11 የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ መሳቢያ ፓምፖች እና ጀነሬተሮች ለማቅረብ የተደረጉ ናቸው፡፡

ከቀሪዎቹ 4 ስምምነቶች ወስጥም ሦስቱ ለ22 ከተሞች 44 ሞተር ሳይክሎችን፣ ማጓጓዝን ጨምሮ 10 ሰርፌስ ፓምፖችን፣ ለ22 ከተሞች ቧንቧዎችና የባንቧ መገጣጠሚያዎችን ለማቅረብ የተደረጉ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ቀሪው አንድ ስምምነት ደግሞ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የመጠጥ ውሃ ችግር ባለባቸው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጠምባሮና ዛላ ወረዳዎች የውሃ ምንጭ ፍለጋ፣ የአዋጭነት ጥናት፣ ዝርዝር ዲዛይን ሥራና በጉድጓድ ቁፋሮ ወቅት የፕሮጀክት አስተዳደርና ቁጥጥር ሥራን ለማከናወን የተደረገ ነው፡፡

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ፣ ለ4 ከተሞች የሚቀርቡት ጠላቂ ፓምፖች ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለተፈናቀሉ ዜጎች ውሃ በማቅረብ ረገድ በየከተሞቹ ያለውን የውሃ እጥረት ለመቅረፍ በአስቸኳይ የሚፈለጉ ስለሆነ በተያዘላቸው የ2 ወር ጊዜ ውስጥ እንዲቀርቡ በአቅራቢው በኩል ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

ቀሪዎቹም ኮንትራቶች በስምምነቶቹ መሠረት ተግባራዊ እንደሚደርጉ ጠቁመው፥ ሚኒስቴሩም ለተዋዋዮቹ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚደርግ ማመልከታውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡