ሚኒስቴሮቹ በአፋር ክልል በአሸባሪው የሕወሓት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአፋር ክልል በአሸባሪው የሕወሓት ኃይል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አድርገዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ አሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ኃይል ወረራ በፈፀመባቸው የአፋርና አማራ ክልሎች ኢ-ሰብኣዊ የሆነና ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠ ድርጊት በንጹሐን ዜጎችና በመሰረተ ልማቶች ላይ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው የመሰረተ ልማቶች ውስጥ የውሃው ዘርፍ አንዱ መሆኑን አውስተው ተቋርጦ የነበረውን የውሃ አቅርቦት ለኅብረተሰቡ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሚሰራው በተጨማሪ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ተቋማቸው ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም በአፋር ክልል በአሸባሪው የትሕነግ ወራሪ ኃይል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የአይነት ድጋፍ በተወካያቸው በኩል ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ያስረከበ ሲሆን ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክቷል፡፡

በሣራ ስዩም (ከግንባር)