ማህበሩ ለአምስት ሚሊየን ዜጎች የምርጫ ግንዛቤ መፍጠሩን አስታወቀ

ሰኔ 11/2013 (ዋልታ) – አምስት ሚሊየን ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በ19 ቋንቋ ስለ ምርጫ ግንዛቤ መፍጠሩን የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መምህራን ማህበር አስታወቁ።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል ጳውሎስ ማህበሩ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

ማህበሩ ከሲቪክ ማህበራት አንዱ መሆኑንና ከምርጫ ቦርድ የመራጮችና ሥነ ዜጋ ትምህርት ለማስተማር ባወጣው ማስታወቂያ መስፈርት ብቁ ሆኖ በመገኘቱ በተሰጠው እውቅና መሰረት ዜጎች ድምፃቸውን በመስጠት የሚስማማቸውን ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲመርጡ ቅስቀሳ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ምርጫ የክልሉ መምህራን ማህበር በተሰጠው ኃላፊነት ልክ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እውን እንዲሆን፣ ዜጎች ድምፃቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የመቀስቀስ ሥራ ሲያከናውን መቆየቱንና ሂደቶቹ መልካም መሆናቸውን አመልክተዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡