ምክር ቤቱ ለ2015 በጀት ዓመት የቀረበለትን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ

ሐምሌ 10/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ለ2015 በጀት ዓመት የቀረበለትን የ100 ነጥብ 05 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ።

የ2015 በጀት ዓመት እቅድ በለውጡ ሂደት የተቀመጡ የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎችን ይበልጥ በማጠናከር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መሆኑን የከንቲባ ጽሕፍት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

ጥራት ያለው ኢኮኖሚ እንዲኖር ማረጋገጥ፣ ምርትና ተወዳደሪነትን በማሳደግ ለዜጎች ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በጥራት ማቅረብ፣ ተቋማዊ ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ፣ የግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚ መሪነት ማረጋገጥ፣ የሴቶችና ወጣቶች ፍትሃዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ መንገድ መሰረተ ልማት፣ የዜጐች ሥራ እድል ፈጠራ፣ የከተማ ውበት ማጠናከር ወዘተ በቀጣይ በጀት ዓመት ትኩረት የሚደረግባቸው መሆናቸውም ተገልጿል።

የታክስ ገቢ ማሳደግ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ፣ ከመንገድ ፈንድ ወዘተ ገቢዎች እድገት ተይዟል።

ከተያዘው በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት የሚውል የካፒታል በጀት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የከተማውን ሕዝብ የልማት ጥያቄና ፍላጎት በዚህ በጀት ብቻ መፍታት እንደማይቻል በመገንዘብ የከተማዋ ነዋሪዎች ለአካባቢ ልማት ሥራዎችና ፀጥታ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቅስ የተቀመጡ ግቦች ለማሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡