ምክር ቤቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

ሚያዝያ 2/2015 (ዋልታ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

በዚሁ መሰረት:-

  1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው በፌዴራል መንግስት የግዢና ንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን በአፈጻጸም ሲያጋጥሙ የነበሩና ለመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ የአሰራር ጉድለቶችን ለማረም፣ የተቋማትን ሃላፊነትና ተጠያቂነት የሚያጎለብት፣ የግዢና ንብረት አስተዳደር ስርዓታችን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን እንዲሁም የአገር ውስጥ አምራቾች በመንግስት ግዢዎች ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ምርታማነታቸው እንዲያድግ ማገዝ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶች በማከል እንዲጸድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2.በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡

በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አዋጅ ቁጥር 1273/2014 ጠቅለል ባለ መልኩ የተደነገጉ ጉዳዮችን በተለይም የፋይናንስ ጉድለት አሸፋፈን፣ የስጋት መቀነሻ ስልቶች እና በተለያዩ እርከኖች ሊኖር የሚገባውን የቋት ክፍፍል በሚመለከት በዝርዝር መደንገግ በማስፈለጉ ፣ አዋጁን ተከትሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የአፈጻጸም ስርዓት እንዲኖር በማድረግ የመድኅን ስርዓቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

ማዕድናት የማይታደሱ የተፈጥሮ ሀብቶች በመሆናቸው መጭዉን ትውልድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል፣ በአካባቢ ጥበቃ መርሆዎች ላይ የተመሰረተና ከስነ-ምህዳር ጋር የሚጣጣም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ የሆነ የማዕድን ሀብት አስተዳደር እና ቁጥጥር ሥርዓት የሚዘርጋ፣ ከውጭ የሚገቡ የማእድን ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት፣ ውጭ በመላክ የሚገኝ የዉጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያግዝ፣ በአጠቃላይ ለአገራችን ኢኮኖሚ እድገት የሚኖረውን አስተዋጾ ማሳደግ በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡