ምክር ቤቱ አስተዳደራዊና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመራበትን ሥርዓት ለመወሰን የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ አጸደቀ

ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) የደቡብ ክልል ምክር ቤት በአዲስ ከሚደራጀው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር የሚኖረው አስተዳደራዊና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመራበትን ሥርዓት ለመወሰን የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ አጸደቀ።
የደቡብ ክልል ምክር ቤት 6ኛው ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤ እያካሄደ ነው።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የመልካም አስተዳደርና አካባቢ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አዳነ ገበየሁ የውሳኔ ሀሳቡን በንባብ አቅርበዋል።
የውሳኔ ሀሳቡ በነባሩ የደቡብ ክልልና 11ኛ ክልል ሆኖ የሚደራጀውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የስልጣን ርክክብ፣ የሃብትና ዕዳ ክፍፍልና ሌሎች አስተዳደራዊና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመሩትን መርሆዎች ለመደንገግ የቀረበ መሆኑ ተገልጿል።
የውሳኔ ሀሳቡ ለሀብት ልየታ፣ ምዝገባ፣ ትመናና ክፍፍል አጋዠ የሆኑ መስፈርቶችን የያዘ ሲሆን በሂደቱ የሚኖር አለመግባባት ችግር ካለ የሚፈታበት አካሄድ የተካተተበት መሆኑ ተገልጿል።
የምክር ቤት አባላት የተለያዩ የማጠናከሪያ ሀሳቦች በመስጠት ሞሽኑን በሙሉ ድምፅ አጽድቀውታል።
በኢትዮጵያ 11ኛው ክልል ሆኖ የሚደራጀው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የካፋ፣ የዳውሮ፣ የሸካ፣ የበንቺ ሸኮ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞኖችና የኮንታ ልዩ ወረዳ በመያዝ የሚደራጅ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።