ምክር ቤቱ ከ3 ሺሕ በላይ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ ወሰነ

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ገረመው ገብረጻዲቅ

ሚያዝያ 15/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ከሦስት ሺሕ በላይ የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ ወሰነ።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ገረመው ገብረጻዲቅ በሰጡት መግለጫ የትንሣኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት ሦስት ሺሕ 141 የሕግ ታራሚዎችን በይቅርታ እንዲፈቱ ወስኗል ብለዋል።

በይቅርታ ከተፈቱት መካከል 3 ሺሕ 85 ወንድ ታራሚዎች ሲሆኑ 56 ደግሞ ሴቶች ናቸው ተብሏል።

በይቅርታ መመሪያው መሠረት ከ10 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል ፍርደኞች፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ አስገድዶ መድፈር፣ በመሠረተልማት ውድመትና ዘረፋ ላይ የተከሰሱ ፍርደኞች በይቅርታ ተጠቃሚነቱ አልተካተቱም።

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም ለ23 ታራሚዎች ተሰጥቶ የነበረው ይቅርታ ተሰርዟል ብለዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።

ይቅርታ ተጠቃሚነታቸው የተሰረዘባቸው ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ በሌላ የወንጀል ድርጊት ተሳታፊ ኾነው በመገኘታቸው መኾኑን አንስተዋል።

በይቅርታ የተፈቱ ታራሚዎች የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና ፍትሕ እንዲሰፍን የበኩላቸውን መወጣት ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።