ምክር ቤቱ የተሻሻለውን የመከላከያ ሰራዊት ረቂቅ አዋጅ አፀደቀ

ሚያዝያ 17/2015 (ዋልታ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለውን የመከላከያ ሰራዊት ረቂቅ አዋጅ በዛሬው ዕለት አፅድቋል።

በረቂቅ አዋጁ የመከላከያ ሰራዊት ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የተጣለበትን ሀገርን የመጠበቅ ተልዕኮ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወጣ ለማድረግና ህብረ ብሔራዊ ተዋፅኦውን የጠበቀ የዘመነ ሰራዊት ለመገንባት ማነቆ የሆኑ የህግ ማዕቀፎችን ለማሻሻል የተካተተበት እንደሆነ ተገልጿል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም እንዲሁም የወደፊቱን ግዳጅ ታሳቢ ያደረገ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱም ተመልከቷል።

ይሁን እንጂ አሁን በስራ ላይ ያሉት አዋጆች በተግባር ሲፈተሹ አዳዲስ አስተሳሰቦችን ስራ ላይ ለማዋል አዳጋች ከመሆናቸውም በላይ በርካታ ክፍተቶች የሚታዩበትና የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ውጤታማነት ላይ ጫና መፍጠሩ ተጠቁሟል።

በመሆኑም ተሻሽሎ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ያሉትን ችግሮችና ክፍተቶች በመሙላት ሊያሰራ የሚችል የህግ ማዕቀፍ፣ አደረጃጀት እና አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችል በመሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን አቢሲ ዘግቧል።