ምክር ቤቱ የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ መረባረብ እንደሚጠበቅ ገለጸ

መጋቢት 28/2014 (ዋልታ) “የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች አዳምጠናል ለመፍትሔው ደግሞ ሁሉም መረባረብ ይጠበቅበታል” ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሰሞኑን በየምርጫ ክልላቸው ተገኝተው ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች መወያየታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ውይይቱ በ4 ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም የሰላምና ፀጥታ፣ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የመሠረተ-ልማትና አጠቃላይ የልማት ጉዳዮችን የተመለከተ ነበር ብለዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው በየምርጫ ክልላቸው የሚገኘው ሕዝብ ሐሳቡን በነጻነት እንዳነሳላቸው ገልጸው ከየማኅበረሰቡ የተነሱትን ጥያቄዎች በየደረጃው ካሉ አስፈፃሚ አካላት ጋር በመነጋገር ግብረ-መልስ ጭምር እየሰጡ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

ከሕዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች እንደከዚህ ቀደሙ በማወያየት ብቻ ይቀራል የሚል ጥርጣሬ ስላለ ሪፖርቱን በማጠናከር በየደረጃው ላሉ አስፈፃሚ አካላት በመላክ ክትትል እና ቁጥጥራቸው ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡