ግንቦት 02/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቦሌ ክፍለ ከተማ የተገነባውን ሁለተኛ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በይፋ ስራ አስጀምረዋል።
አንዳችን ለሌሎች የተስፋ ብርሃን በመሆን መደጋገፍ እና መረዳዳት ይገባል ያሉት ምክትል ከንቲባ፣ ከኮቪድ ወረርሽን ጊዜ ጀምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የመደገፍና የመርዳት ተግባራት ሲከናወኑ መቆየቱን ገልጸዋል።
ያለንን ሃብት በአግባቡ ካዋልን ብዙ ችግሮቻችን መቅረፍ እንችላለን ያሉት ወ/ሮ አዳነች፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ዛሬ ተመርቆ የተከፈተው ተስፋ ብርሃን ምገባ ማእከል በቀን አንድ ጊዜ ከ1 ሺህ በላይ ዜጎችን መመገብ ያስችላል ብለዋል፡፡
መንግስት ከለውጡ ወዲህ ዜጎቻችን ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች እየሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ፣ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ምገባ ማእከሉ ዜጎችን መመገብ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ስልጠናም አግኝተው ራሳቸውን እንዲችሉም ማእከሉ ይሰራል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩም አቅም የሌላቸው ዜጎችን ለመርዳት ፍላጎት ያላቸውን በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶችን እና ተቋማትን በማስተባበር በአምስት ክፍለ ከተሞች በቋሚነት የምገባ ማዕከል የማደራጀት ስራ ተሰርቷልም ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራርና ሰራተኞች፣ ቴምፕል ኦፍ ጋድ ቤተክርስቲያን እንዲሁም ስካይ ላይት ሆቴል በቦሌ ክፍለከተማ ስራ የጀመረውን ተስፋ የምገባ ማእከል ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬተሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፋሲካ እለት በአራዳ ክፍለ ከተማ ከ1ሺህ በላይ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የምገባ ማዕከል በይፋ ስራ ማስጀመሩም ይታወሳል።