ምክትል ጠ/ሚ/ር ደመቀ መኮንን ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

ጥር 19/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዛሬው ዕለት የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር የሆኑትን አብዲሰዒድ ሙሴ አሊን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ መንግስት ሰራዊቱን ወደ ትግራይ ክልል አንዳይገባ ያስተላለፈውን ውሳኔ፣ እስረኞች በመፍታት የወሰደው እርምጃን እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅቶች መካሄዱን አሰመልክተው ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል።

ከእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ አስፈላገውን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ቢሆንም የሽብር ቡድኑ ግን በቅርቡ በአባላ በኩል አዲስ ጥቃት በመከፈት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱን እያወከ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ ደንታ የሌለው ሃይል መሆኑን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።

ሶማሊያ በዓለም አቀፍ መድረኮች በተለይም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ሶማሊያ ትክክኛ አቋም በማራመዷ ምስጋና ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አብዲሳኢድ ሙሴ አሊ በበኩላቸው በሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለተሰጣቸው ዝርዝር ማብራሪያ አመስግነው፣ የሁለቱን ሀገራት ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።