ምክትል ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የእምነበረድና የቀርከሃ ፋብሪካዎችን ጎበኙ

ሰኔ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የእምነበረድና የቀርከሃ ፋብሪካዎችን ጎበኙ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው እየጎበኙ ሲሆን በዛሬው እለትም የእምነበረድና የቀርከሃ ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን፣ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝና ሌሎችም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ከሀገራዊ ለውጡ በኃላ ሰላምን በማፅናት ያለውን የማዕድንና የቀርከሃ እምቅ አቅም ለመጠቀም የተጀመረውን ሥራ አድንቀዋል።

በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መኖሩን ተመልክተናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ የግብርና ሥራዎች በተለይም የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር የአረንጓዴ አሻራ አፈጻጸምን በትናንትናው እለት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የክልሉን እምቅ አቅም ለልማት በማዋል የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበው በክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ኃብትና ምቹ የአየር ሁኔታ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት መሠረት የሚሆን ንቅናቄ መኖሩንም ጠቁመዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው በክልሉ የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ግራናይትን ጨምሮ ሰፊ የማዕድን ሀብት መኖሩን ጠቅሰው፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እነዚህ አቅሞችን ወደ ልማት በማዋል ረገድ አበረታች ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡