ምዕራብ ዕዝ ከህግ ማስከበር እስከ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻ ከፍተኛ ድል ያስመዘገበ ነው – ጀኔራል አበባው ታደሰ

መጋቢት 12/2014 (ዋልታ) “ምዕራብ ዕዝ ከህግ ማስከበርና የኅልውና ዘመቻው እስከ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻ ከፍተኛ ድል ያስመዘገበ ነው” ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ተናገሩ።

በምዕራብ ዕዝ ለሠራዊቱ አመራሮች የወታደራዊ ሳይንስ እና የአመራር ጥበብ ስልጠና ተሠጥቷል።

ጀኔራል አበባው ታደሰ በዚሁ ወቅት ተገኝተው እንደገለጹት ምዕራብ ዕዝ የሠራዊት አባላት እና አመራሮች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በድል በመወጣት ሀገርን ከብተና፤ ሕዝብን ከእልቂት እና ስቃይ መታደግ ችለዋል።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የከፈተውን ጦርነት መቀልበስ የተቻለው ከአመራር እስከ ታችኛው የሠራዊት አባል ባለው የሀገር ፍቅር ስሜት እና ቁርጠኝነት ነው ብለዋል።

“አመራር ሁለገብ ብቃት እና ልምድ ሲኖረው የሚመራውን ክፍል በስልጠና ያዘጋጃል” ያሉት ጀነራል አበባው ሠራዊት ሰልጥኖ ለግዳጅ ዝግጁ ሆኖ ሲጠብቅ ውጊያን በአጭር ጊዜ እና በአነስተኛ ኪሳራ ድልን ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል።

“የዕዙ አመራሮች በስልጠና ያገኛችሁትን ወታደራዊ የአመራር ጥበብ ወደ ተግባር በመለወጥ ቀጣይ ለሚሰጣችሁ ግዳጅ ራሳችሁን እና ሠራዊቱን ማዘጋጀት ይኖርባችኋል” ሲሉ መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።