ም/ጠ/ሚኒስትሩ በአገሪቱ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል አሉ

ታኅሣሥ 5/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው ሕወሓት ላይ መንግሥት እየወሰደ ካለው የተጠናከረ የፀረ ማጥቃት እርምጃ ጎን ለጎን በአገሪቱ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቋቋም እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

የብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ እና መልሶ ማቋቋም ተልዕኮ ዙሪያ ለመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ግልፅ የሥራ ስምሪት የሰጠበት መድረክ አካሄዷል።

የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደመቀ መኮንን በጠላት ወረራ ተይዘው የተለቀቁ፤ ለጊዜው በጠላት እጅ ባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በአርብቶ አደሩ አካባቢ የደረሰውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም የሚያስችሉ ሁሉን ዐቀፍ ድጋፎች በልዩ ትኩረት ይከናወናሉ ብለዋል።

በአገሪቱ ለተከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በሚሰጡ ምላሾችና የመልሶ ማቋቋም ተግባራት ዙሪያ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት በጋራ ሊረባረቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ካላት መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ እና የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔሃብታዊ እና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጋላጭ እንደሆነችም አብራርተዋል።

በመሆኑም በገጠር አርሶ አደሩ ፈጥኖ ወደ በጋ የግብርና ሥራ እንዲገባ መስኖ ባለባቸው አካባቢዎች የተለያዩ አስፈላጊ የእርሻ ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራዎች እንደሚከናወኑ መጠቆማቸውንም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።