ም/ጠ/ሚኒስትሩ ከቡርኪናፋሶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

ሐምሌ 4/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቡርኪናፋሶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦሊቪያ ሮምባ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ግንኙነት ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ የተጀመረ መሆኑን አንስተው በቀጣይ ግንኙነቶች ሊታደስ ይገባል ብለዋል።
ስለ ኢትዮጵያ ወሳኝ ጉዳዮችን በተመለከተ በተለያዩ መድረኮች ላይ ቡርኪናፋሶ ያሳየችውን ወጥ እና ሚዛናዊ አቋምም አድንቀዋል።
ሁለቱ ሀገራት በአቅም ግንባታ ላይ ብዙ ያልተነኩ እምቅ አቅም ያላቸው በመሆኑ ግንኙነታውን ለማሻሻል መንገድ የሚጠርግ መሆን አለበት ብለዋል።
ኦሊቪያ ሩዋምባ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቡርኪናፋሶ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማዕከል ሆና መቆየቷን ጠቅሰው የኢትዮጵያ አስፈላጊነት ከመልክአ ምድራዊ ስፋቷ በላይ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ አያይዘውም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ኩራት መሆኑን ገልጸው የግድቡ መገንባት የውስጥ ሃብቶችን በመጠቀም ለአፍሪካ ፍፁም የዕድገት ምሳሌ እንደሚሆን መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።