ም/ጠ/ሚኒስትሩ ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተውያዩ

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአሜሪካን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመርን ጋር ተወያዩ።

ሚኒስትሩ መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየወሰዳቸው ያሉ ርምጃዎችን ገለጻ አድርገዋል።

በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ አማካኝነት ለተጀመረው የሰላም ጥረት መንግሥት ቁርጠኛ ነው ያሉ ሲሆን መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ተደራዳሪ ቡድን አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም ገልፀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተኩስ አቁም ስምምነቱ፣ ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ ተጀራሽነት እና ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉም ለልዩ መልዕክተኛው ገልፀዋል።

መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ሙሉ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ባለበት ወቅት የህወሓት ቡድን በተቃራኒው እያሳያ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል የሚፈጥር በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቡድኑ ላይ ጫና ሊያሳርፍ ይገባል ብለዋል።

የሕዳሴ ግድቡን የሦስትዮሽ ድርድር በተመለከተ ከልዩ መልዕክተኛው ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ ድርድሩ በመርህ ላይ ተመስርቶ ፍሬያማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያላትን ፅኑ አቋም ገልፀዋል።

የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በበኩላቸው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉትን እርምጃዎች አድንቀው የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት ላይ እየታየ ያለው ለውጥ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!