ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሩሲያ እና ከማሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

መስከረም 14/2015 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሩሲያ እና ከማሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በሁለትዮሽና ዓለም ዓቀፍ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 77ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ሁለትዮሽ እና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የሚያጠናክር ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ።

ከሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉ ወቅት የተደረሱ መግባባቶች ያሉበት ደረጃ ላይ የተነጋገሩ ሲሆን የሁለቱ አገራት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድም ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከማሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዶሌይ ዲኦፕ ጋር ባደረጉት ውይይት የአፍሪካን ህብረት በማጠናከር የአህጉሪቱን ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚገባ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW