ም/ጠ/ሚ ደመቀ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ገለጻ አደረጉ

ነሐሴ 26/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ላደረጉ አምባሳደሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮችና የሚሲዮን መሪዎች ገለጻ አደረጉ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተናጥል ተኩስ አቁም በማወጅ ለሰላም ቢሰራም ህወሀት ግን ራሱን ለዳግም ጦርነት በማዘጋጀት በአፋርና በአማራ ክልል ወረራ በመፈጸም ጥቃት እያደረሰ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ መንግስት በህወሀት የሚሰነዘረውን ጥቃት እየመከተ ለሰላም እጁን አላጠፈም ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ጥቂት ሀገራትና ግለሰቦች የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በሚጻረን መልኩ ለህወሃት ብዙ እርቀት ሄደው ድጋፍ እያደረጉ እንዳሉ ጠቁመው ለአብነት ለሽብር ቡድኑ የጦር መሳርያ ሊያቀብል የነበረ አውሮፕላን በኢትዮጵያ አየር ሀይል መመታቱን ገልጸዋል፡፡

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ  እና ሚዛናዊ በመሆን  ከእውነታው ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሸባሪው ህወሀት በዜጐች ላይ ዳገም ጥቃት እያደረሰ መሆኑንም በመግለጽ መንግስት የዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ ህገ መንግስታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ይገደዳል ብለዋል።

በመስከረም ቸርነት