ም/ጠ/ር ደመቀ መኮንን ኅዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት ሥራ በመጀመሩ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

የካቲት 13/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት ሥራ በመጀመሩ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

በመልዕክታቸውም የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ወደ ኋላ ያለፈባቸው የታሪክ አንጓዎች ሁሌም በደማቁ ይታወሳሉ ብለዋል፡፡

ገና ከመነሻው ፕሮጀክት “ⵝ” በሚል መነሻ ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት የነበረው የግንባታ ሃሳብ በይፋ መሰረት ድንጋይ ተቀምጦ ወደ ስራ ተገብቷል ፤ በሂደትም ለግንባታ ስራው ያመች ዘንድ የአባይ ወንዝ የሺህ ዓመታት ጉዞውን በጊዜያዊነት አቅጣጫው ተቀይሮ የግድቡ ግንባታ በትኩረት ሲከናወን መቆየቱን አንስተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደትን ተከትሎ የመጀመሪያውና ሁለተኛው የሙሌት ምዕራፍ በተከታታይ መካሄዱን አንስተው ለሺሕ ዓመታት ብዙ ኪሎ ሜትሮች ሲጓዝ የነበረው የዓባይ ወንዝ የተወሰነው ጊዜ ብሎ “አረፍ ብሎ” ኃይል በማመንጨት ጉዞውን ቀጥሏልም ነው ያሉት፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ሕዝብ የተባበረ ድጋፍ እና ተሳትፎ፣ የባለሙያዎች ጥረት እና የአመራር ጥበብ በደረሰበት የግንባታ ደረጃ እና የቴክኖሎጂ ልማት ተርባይኑ የቅድመ ኃይል ወደ ማመንጨት መሸጋገሩን አንስተዋል፡፡

እነሆ ዛሬ ችቦው በራ! ወሳኝ እና ውስብስብ ተግባራትን ተሻግሮ እዚህ ደረጃ በቅቷልም ነው ያሉት፡፡

ለዚህ ታሪክ እውን መሆን አሻራችሁን ያሳረፋችሁ ባለሙያዎች፣ ሕዝባዊ ተሳትፎውን ያስተባበራችሁ አካላት፣ በሃገር ቤት እና በውጭ የምትኖሩ መላው የኢትዮጵያዊያን በሙሉ እንኳን ደስ አለችሁ፤ ደስ አለን ብለዋል፡፡

‘‘እንደጀመርነው ለዚህ አብቅተናል፤ በአጭር ጊዜ ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ወደተሟላ ድርብርብ ድል እናሸጋግረዋለን ፤ ስናብር ስናምር! ይለዋል እንዲህ ነው!’’ ብለዋል፡፡

የቀደሙ አባቶቻችንን ነፃነት ከማውረስ ጀምሮ አኩሪ ታሪክ ሰርተው አልፈዋል ፤ ይህ ትውልድ ዕድለኛ ሆኖ አኩሪ ገድል ፈፅሟል ፤ ለመጪው ትውልድም ታሪካዊ መደላድሉን አኑሯም ነው ያሉት፡፡

እርግጥ ነው! ይህን አኩሪ ገድል እየሠራ ያለ ሕዝብና አመራር በሌሎች አጥፊና አፍራሽ ድርጊቶች ሲፈተን ማስተዋል ግራ ማጋባቱ አይቀሬ ነውም ነው ያሉት፡፡

እንዲህ አይነት ገናና እና አኩሪ ታሪክ በሚሰራ ሃገር እና ሕዝብ መሃል ሃገር የካዱ ባንዳዎች ንፁሃንን የማጥቃት እና ሃገር የማፍረስ ተልእኮ ውስጥ ተሰማርተው ማየት የእናት ሆድ ዝንጉርጉርነትን በገሃድ የሚያሳይ ነውም ብለዋል፡፡

አንዳንድ ባንዳዎችና ጨካኞች ለጊዜው ብዙ ዋጋ እያስከፈሉን ቢሆንም ፤ በሁሉም ማዕዘናት ያሉ ኢትዮጵያዊያን በየዘመኑ የሚገጥማቸውን ፈተና በድል እየተሻገሩ እንደህዳሴ ግድባችንና ሉዓላዊነትን የማስከበር ተልዕኮን በጋራ ለማስፈፀም ወደፊት እየተመሙ መጓዛቸውን ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡

በግልፅ እንደሚታወቀው ከቀደሙት አባቶቻችን የወረስነው ታሪክ ይኸው ነው ፤ እኛ ደግሞ በተግባር እየሰራነው ያለው ይህንኑ የሚያፀና ነው ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ለመጪው ትውልድ ትልቅ አሻራ በማኖር በሁሉም መስክ ታላቅነታችንን የበለጠ በጋራ እውን ለማድረግ እንድንረባረብ አደራም ብለዋል፡፡

ለዚህ ድል ላበቃችሁን ሁሉ እናመሰግናለን ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክታቸውን አስፍረዋል፡፡