ሠራዊት በሀገራችን ላይ የሚቃጡ ትንኮሳዎችን መመከት የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠሩን የምዕራብ ዕዙ ምክትል አዛዥ ተናገሩ

ሐምሌ 29/2014 (ዋልታ) በምዕራብ ግዳጅ ቀጠና ተልዕኮውን እየፈፀመ ያለው የሠራዊት ክፍል ከውስጥም ይሁን ከውጭ በሀገራችን ላይ የሚቃጡ ትንኮሳዎችን መመከትና መቀልበስ የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አስተማማኝ ዝግጁነት መፍጠሩን የዕዙ ምክትል አዛዥ ተናገሩ።

ጀነራል መኮንኑ በአውደ ውጊያ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት በየደረጃው ያለ አመራር ቅንጅት፣ ቁርጠኝነትና ጠንካራ አመራር ሰጪ መሆን የማይተካ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

አትሌቶቻችን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባደረጉት ትንቅንቅና ተጋድሎ ያስመዘገቡትን ድል በመጥቀስ ኢትዮጵያ አዲሱን በጀት ዓመት በድል ጀምራለች ያሉት ምክትል አዛዡ ድሉን በሁሉም የስራ መስክ በማስቀጠል የኢትዮጵያን ከፍታ ማረጋገጥ እንደሚገባ አንስተዋል።

ጠላት ሀገርና ህዝብን ሊያዋርድ አቅሙን አሟጦ ሲፍጨረጨር በመጠንከራችን ጠላትን ከፍላጎቱ በታች ማድረግ ችለናል ብለዋል።

በዚህ ሂደት በየደረጃው ያለ አመራር ሚና የማይተካ እንደነበር በመጥቀስ አመራሮች አቅማቸውን በቀጣይነት አዳብረው የክፍሎቻቸውን አቅም በማሳደግ ለተሻለ ግዳጅ ማዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ምክትል አዛዡ አክለውም አመራሮች የሚመሩትን ሰራዊት የማድረግ አቅምና የዝግጁነት ደረጃ ለማሳደግ የሚያግዙ የመሪነት ክህሎትን የሚያዳብሩ ተግባራትን ማከናወን አለባቸው ማለታውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ አመላክቷል።