ሪሺ ሱናክ በይፋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) ትላንት በእንግሊዝ ምክር ቤት የወግ አጥባቂ ፓርቲ ተወካዮች በሰጡት ድምጽ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ሪሺ ሱናክ ዛሬ በይፋ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡

ሱናክ ዛሬ የእንግሊዙን ንጉስ ቻርለስ አግኝተው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩስ የስልጣን መልቀቂያቸውን ካስገቡ በኋላ ነው በይፋ ጠቅላይ ሚኒትር ሆነው የተሸሙት፡፡

ሱናክ ንጉስ ቻርለስ ወደ ንግስና ከመጡ በኋላ የመጀመሪያው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ ይህ ሹመት እንግሊዝ በሰባት ሳምንታት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር መቀያሯን ያረጋገጠ ሆኗል፡፡

ሱናክ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ባደረጉት የመጀመሪያው ንግግር እንግሊዝ ስር በሰደደ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መሆኗን ጠቅሰው ቀውሱ እንዲከሰት ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ቃል ገብተዋል፡፡

በ200 ዓመታት ወስጥ እንግሊዝን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ካገለገሉ ሰዎች ውስጥ የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ሱናክ ወጣቱ ናቸው፡፡