ርዕሠ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የተሳተፉ ዜጎችን አመሰገኑ

መጋቢት 21/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሠ መስትዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዘንድሮው የክልሉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የተሳተፉ ዜጎችን አመሰገኑ።
ርዕሠ መስተዳድሩ በምስጋና መግለጫቸው የክልሉ መንግሥት የኦሮሞ ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብሩን በማጠናከር ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
“ሕዝባችን በአዳዲስ የልማት ሃሳቦች የተደገፉ የልማት ዕቅዶች ሲቀርቡለት ተዓምር መስራት እንደሚችል አሳይቷል” ያሉት ርዕሠ መስተዳድሩ “በመደመር መንገድ የሁሉንም ብልጽግና እናረጋግጣለን የምንለውም በሕዝባችን ትልቅ ተሥፋ ስላለን ነው” ብለዋል።
“የበጋ ስንዴ ምርትም ከባዕዳን እጅ ሊያድነን እንደሚችል ሕዝባችን በሠራቸው የልማት ሥራዎች አረጋግጧል” ነው ያሉት።
በዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ሕዝቡ በመንግሥት በጀት መሸፈን የማይችሉ የበርካታ ቢሊየን ብር የሚገመት ሥራንም ሰርቶ ማሳየቱን ገልፀዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የገዳ ሥርዓት በሕዝቡ ውስጥ የኖረ እና የሚተገበር በመሆኑ ህጋዊ መሠረት ለማስያዝ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት።
በመረዳዳት ባሕል በሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ መጥፎውን ጊዜ እያሳለፈ አንደሚገኝ በመግለፅ ሕዝቡ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተራቡትን በመመገብ ደግነትን በማሳየቱም አመስግነዋል፡፡
በዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ዕቅድ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ በመሥራት 2 ነጥብ 41 ሚሊየን ሄክታር መሸፈን መቻሉንና ጉልበቱም በገንዘብ ሲተመን ከ9 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚሆን ነው ይፋ ያደረጉት።
ይህም በኅብረ ብሔራዊ አንድነት የልማት ድል ማስመዝገብ የጀመረው ሕዝብ ወደ ብልጽግና ለሚያደርገው ጉዞ ስኬት ማሳያ መሆኑን መግለጻቸውን የኤፍቢሲ ዘገባ አመላክቷል፡፡
የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ውጤታማ ለማድረግ የችግኝ መትከያ ቦታ በማዘጋጀት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።