ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን አስጀመሩ

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሰኔ 27/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በክልሉ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን አስጀመሩ።

በክልሉ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ፈተና 4 ሺሕ 900 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ተገልጿል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ፈተናውን ባስጀመሩበት ወቅት በክልሉ ለፈተናው አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው በተለይም በተማሪዎች መካከል ኩረጃ እንዳይኖር፣ ፈተናው እንዳይሰረቅ እና የፈተናው አሰጣጥ ውጤታማ እንዲሆን ከማስቻል አንፃር በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ለትምህርት ጥራት በተለይም የተማሪዎች ውጤት እንዲጎለብት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተው የሚመለከታቸው አካላትም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በክልል ደረጃ በከተማና በገጠር በሚገኙ 24 የፈተና ጣቢያዎች ፈተናው እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW