ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ከተለያዩ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ገለጹ

መጋቢት 15/2014 (ዋልታ) ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በአሸባሪው ሸኔ የተፈናቀሉ 692 ሺሕ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከክልል አመራሮች ጋር በመነጋገር እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የ2014 ዓ.ም የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤት አባላት አቅርበዋል፡፡

አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው የኅልውና ዘመቻ እንደ ሕዝብ በመነሳት፣ የፀጥታ ኃይሉን በማጠናከር፣ ሚሊሻውንና ፋኖውን በማቀናጀት መቀልበስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዘመቻው የሎጀስቲክስ ወጪ ግማሹ ሕዝብን በማስተባበር የተገኘ ሲሆን በዚህም 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ፤ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ደግሞ የአይነት ድጋፍ መደረጉ ተነግሯል፡፡

በአሸባሪው ትሕነግ ከተፈናቀሉት መካከል ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ወደ ቀያቸው በመመለስ እና በቀያቸው ሆነው ችግር ላይ ለወደቁ 9 ሚሊዮን ዜጎች የሰብኣዊ ድጋፍ ማድረግ መቻሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በክልሉ ባለፋት 6 ወራት 16 ቢሊዮን ብር መዋለ ንዋይ ያስመዘገቡ 310 ባለሀብቶች ፈቃድ መውሰዳቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርቱ ገልጸዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር በክልሉ በ10 ከተሞች ላይ 125 ሄክታር የሳይት ፕላን ለመስራት እንቅስቃሴ በመጀመር በ6 ከተሞች 69 ሄክታር መሬት ከ3ኛ ወገን ነፃ መደረጉንም አንስተዋል።

ምንይሉ ደስይበለው (ከባሕር ዳር)