ሰራተኞች እያሳዩት ያለው መዘናጋት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲስፋፋ እያደረገ ነው- የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን

ግንቦት 02/2013 (ዋልታ) – የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጥንቃቄዎች ላይ ሰራተኞች እያሳዩት ያለው መዘናጋት ወረርሽኙ እንዲስፋፋ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ገለጸ።

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ እንደገለጹት፣ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ቢቀጥልም በሰራተኞች እንዲሁም አጠቃላይ በማህበረሰቡ ዘንድ መዘናጋት ይስተዋላል።

በመሆኑም የወረርሽኙ መስፋፋትና በቫይረሱ የሚያዙ ሰራተኞች እየተበራከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

“የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በሚመለከት በሰራተኛው ዘንድ የመዘናጋት ሁኔታዎች ይታያሉ፤ መዘናጋት በመኖሩ እንደ ሀገር የቫይረሱ ስርጭት አሁን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ያለው” ብለዋል።

ከሰራተኞች ባሻገር ተቋማት ወረርሽኙን ለመከላከል ከዚህ ቀደም ያደርጉ የነበሩት ጥንቃቄ አሁን ላይ ተቀዛቅዞ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ በትራንስፖርት አገልግሎት፣ በካፌና ሬስቶራንቶች፣ በመዝናኛ ስፍራዎችና በሌሎችም አካባቢዎች የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገው ጥንቃቄ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም በፋብሪካዎች ላይ የሚከናወኑ ስራዎች ለንክኪ የተጋለጡ በመሆናቸው በስራ አካባቢዎቻቸው የሰዎችን ንክኪ በመቀነስ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን በአግባቡ በመጠቀምና ርቀትን በመጠበቅ መስራት ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል ክትባቶች እየተሰጡ ቢሆንም ጎን ለጎን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መግባቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በአጠቃላይ ከ262 ሺህ በላይ ዜጎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፣ ከ3 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።