ሳፋሪኮም በአዳማ እና ባሕር ዳር የደንበኞች ኔትወርክ አገልግሎት ሙከራ ጀመረ

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ

መስከረም 2/2015 (ዋልታ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአዳማ እና ባሕር ዳር ከተሞች ተከታታይ የደንበኞች የኔትወርክ አገልግሎት ሙከራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

በከተሞቹ ደንበኞች በ07 በሚጀምረውን የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መስመር የስልክ ቁጥሮቻቸውን መርጠው ሲም ካርድ መግዛት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሲም ካርድ ደንበኞች ኔትወርኩን ለአንድ ወር ያህል እንዲሞክሩት የሚረዳ የደንበኝነት ማስጀመሪያ የዳታ፣ ድምጽ እና ጽሁፍ መልዕክቶች ጥቅል የያዘ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ደንበኞች የሲም ካርድ ሽያጭ ምዝገባ፣ የአየር ሰዓት እና የስልክ ቀፎዎች ግዢ እንዲሁም የደንበኞች ድጋፍ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መለያ ከተለጠፈባቸው መደብሮች እና ሱቆች ማግኘት እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡

በሙከራ ኔትወርኩ ደንበኞች ዳታ መጠቀም፣ ጥሪዎች እና የጽሁፍ መልዕክቶችን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ከኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ጋር መለዋወጥ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ጥሪዎች ማድረግ እንደሚችሉ ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW