ሴናተር ኪም ጃክሰን በሕወሓት የሀሰት መረጃ በመታለል ኢትዮጵያ ላይ ስለነበራቸው አቋም ይቅርታ ጠየቁ

ሚያዝያ 10/2014(ዋልታ) በአሜሪካ የጆርጂያ ሴናተር ኪም ጃክሰን በሕወሓትና ደጋፊዎቹ ፕሮፖጋንዳና የሀሰት መረጃ በመታለል አለአግባብ ኢትዮጵያ ላይ ለወሰዱት የተሳሳተ አቋም ይቅርታ ጠየቁ፡፡
ሴናተሯ ይቅርታ የጠየቁት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ሲሆን ሴናተር ኪም ከኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያዊያን ስለጦርነቱ እውነታና መሬት ላይ ስላለው ሃቅ እንዳስረዷቸው ገልጸዋል።
በአሜሪካ የጆርጂያ ሴናተር ኪም ጃክሰን በተለያዩ የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች እና በኢሜል በሚደርሱኝ መልዕክቶች ኢትዮጵያዊያን ከትግራይ ሕዝብ ጋር ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለባቸው አሳውቀውኛል፤ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን እና ጓደኞቻችን ናቸው ሲሉም በተደጋጋሚ በኢሜል ገልጸውልኛል ብለዋል፡፡
እኔም አሁን የደረስኩበትን እውነታ ከግምት ሳላስገባ ቀድሞ በደረሰኝ የሕወሓት ደጋፊዎች ሀሰት መረጃ ብቻ የተሳሳተ አቋም ይዤ ነበር ሲሉም አክለዋል፡፡
እውነታውን እንዳይ ስላደረጋችሁ አመሰግናለሁ ያሉት ሴናተሯ ለፈጠርኩት ስህተትም ሙሉ ኃላፊነት ወስጄ ለማረም እሠራለሁ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትንና ሕዝቡን ይቅርታ እጠይቃለሁ ነው ያሉት ባደረጉት ንግግራቸው፡፡