ሶማሌ ክልል ያለው ሰላም ክልሉ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆኑ ተገለፀ

ነሀሴ 20/2013 (ዋልታ) – በሶማሌ ክልል ያለው አስተማማኝ ሰላም ክልሉለኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆኑን እንደሚያሳይ የኬንያ ሪፐብሊክ የፓርላማ አባላት ገለፁ፡፡
በክልሉ የተለያዩ ከተሞችን ጉብኝት ያደረጉት አባላቱ ከጎበኟቸው አካባቢዎች መካከል የጅግጅጋ ከተማ እና የጎዴ ከተማ የሚገኙበት ሲሆን ባለፉት ሶስት አመታት በከተሞቹ የተከወኑ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
በጎዴ ከተማ በነበራቸው ቆይታ በሸበሌ ወንዝ አማካኝነት የሚለማው የስንዴ ማሳ፣ የምዕራብ ጎዴ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት፣ በሸበሌ ወንዝ ላይ የተሰሩ ግድቦች፣ በጎዴ ከተማ ላለፉት ሶስት አመታት የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን፣ ከሸበሌ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ጋርም ተገናኝተው ተወያይተዋል።
የፓርላማ አባላቱ ከጉብኝታቸው በኋላ ዛሬ ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድና ከአቶ ኢብራሂም ዑስማን እና ከክልሉ ከፍተኛ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር ምክክር አድርገዋል።
በውይይታቸው ልዑኩ በአጠቃላይ በሶማሌ ክልል ያዩት ነገር ሁሉ እንዳስደስታቸው ገልፀው ከዚህ በፊት ስለ ሶማሌ ክልል የነበራቸው የተዛባ አስተሳሰብ መቀየሩን መናገራቸውን ከሶማሌ ክልል ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡