ቀዳሚው ተግባራችን የሚሆነው ህልውናችንን ማስጠበቅ ነው አሉ የደቡብ ክልል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች

አርባ ምንጭ ነሃሴ 07/2013 (ዋልታ) – የሀገር ህልውና ሳይረጋገጥ ተፎካክሮ ሀገርን መምራት የሚቻል ባለመሆኑ አሁን ላይ ቀዳሚው ተግባራችን የሚሆነው ህልውናችንን ማስጠበቅ ነው አሉ በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች::
17 ተፎካካሪ ታርቲዎች በሀገራዊ የህልውና ዘመቻው ላይ በጋራ መንቀሳቀስ በሚችሉበት ሁኔታዎች ዙሪያ በአርባምንጭ ከተማ ውይይት አካሂደዋል::
አስቀድሞ ወቅታዊውን የአረንጓዴ አሻራ በማኖር ምክክራቸውን የጀመሩት ተፎካካሪዎቹ ፖርቲዎች በውይይታቸው መነሻ ሀሳብ በሆነው የሀገርን ህልውና መታደግ ጊዜ ወስደው መክረዋል::
የሀገር ህልውና ከየትኛውም የፖለቲካም ይሁን ሌሎች ልዩነቶች ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ያሉት የጋራ ምክር ቤቱ አባት ሀገራችን በታሪኳ ጥቂት የለውጥ እድሎችን ብታገኝም ከስኬት ሳይደርሱ ቀርተዋልብለዋል:: አሁን የተገኘውን የለውጥ እርምጃ የሚፈታተኑ አሰላለፎች በመፈጠራቸው በጋራ መቆም ይገባል ሲሉ አክለዋል::
ሀገራችን በዚህ ፈታኝ ወቅት ለውጡን በማስቀጠል በተለይ 6ተኛው ዙር ምርጫን በስኬት በማጠናቀቅና የ2ዙር የህዳሴው ግድብ ውሀ ሙሌትን እውን ማድረግ መቻሉ ትልቅ ግምት ነው የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል፡፡
“ሀገር ስትኖር ነው አሸንፎ ስልጣን መያዝ የሚቻለው ያሉት ተወያዮች በውስጥም በዉጭም የተሰለፈውን የጠላት ሀይል በጋራ ለመመከት በሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምንሰለፍ ልናረጋግጥ እንወዳለን”” ሲሉ የተፎካካሪ ፖርቲ ተወካዮች ተናግረዋል::
በገዢው ፓርቲ የተሠገሠጉ ዉስጣዊ ባንዳዎችን ማስታገስ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ የተጠቆመ ሲሆን አሁን የታየው አይነት ቀውስ በቀጣይ እንዳይከሰት ህግና ስርአትን በተከተለ መልኩ እልባት መስጠት እንደሚገባም ተወስቷል::
በመጨረሻም ተፎካካሪ ፖርቲዎቹ የአቋም መግለጫ በማውጣት ውይታቸውን መቋጨታቸውን ዘጋቢያችን ክብሩ ዋና ከአርባ ምንጭ ያደረሰን ዘገባ ያስረዳል፡፡