ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ማዕከል ያደረጉ የሳይበር ጥቃቶች በኢትዮጵያ ላይ መሞከራቸው ተገለጸ

ሐምሌ 25/2014 (ዋልታ) ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ማዕከል ያደረጉ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ የሳይበር ጥቃቶች በኢትዮጵያ ላይ መሞከራቸውን እና ከዚህም ውስጥ 97 በመቶ የሚሆኑትን ማክሸፍ መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አስታወቀ፡፡

የአስተዳደሩ ም/ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ እንደተናገሩት በ2014 በጀት አመት ከተቃጡ 8 ሺ 985 የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ 45 ከመቶ የሚሆኑት ቁልፍ የሀገሪቱን መሰረተ ልማት ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውም ጠቅሰዋል።

የጥቃት ሙከራዎች ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል የፋይናንስ ተቋማት፤ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች፣ ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የመንግስት የፖለቲካ አደረጃጀቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የጤና ተቋማትና የግል ድርጅቶችም ይገኙበታል ብለዋል ፡፡

በበጀት ዓመቱ 99 ተቋማት ላይ የሳይበር ደህንነት ፍተሻ እና ግምገማ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም ተቋማት ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉባቸውን በርካታ ክፍተቶች ፈልጎ ማግኘት እና እንዲታረም መደረጉንም ምክትል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

የሳይበር ዓለም ተለዋዋጭ እና ኢ-ተገማች መሆኑን በመጥቀስም ከዚህ በኋላም ከበድ ያሉ የሳይበር ጥቃቶች ሊደርሱ ስለሚችሉ ሁሌም ዝግጁ ነን ማለታቸውን የኢፕድ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ቴክኖሎጂዎች ላይ ስትራቴጂካል ጥናትና ምርምር ማስቀጠል እንዲሁም ከተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሥራትና ዜጎቻችንን በማንቃት የሀገራችንን የዲጂታል ሉዓላዊነትና ሳይበር ዲፕሎማሲያችንን በጋራ ልናስጠብቅ ይገባል ብለዋል።