ቋሚ ኮሚቴው ለግጭት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ጥናት እንዲደረግ አሳሰበ

ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ለግጭት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እና ሁኔታዎች ላይ ጥናት እንዲደረግ አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያውን የሰጠው፤ የሰላም ሚኒስቴርን የሥራ እንቅስቃሴ ከተመለከተ በኋላ ባስቀመጠው አቅጣጫ ነው፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)፤ ሚኒስቴሩ ባለፉት ሃያ እና ሠላሳ ዓመታት የነበሩ ግጭቶች ምንጮቻቸውን እና የአፈታት ሥርዓታቸውን በማጥናት ላይ ትኩረቱን ማሳረፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች እንዳሉ አስታውሰው የግጭት አፈታቶቹ ምን ያህል ውጤት አምጥተዋል የሚለው ሊጠና ይገባል ብለዋል፡፡
በተቋሙ የሰላም ኤግዝቢሽን ማዕከል የጋሞ አባቶችን ነባር እና ባሕላዊ የዕርቀ-ሰላም መንገድ የሚያሳየውን፤ ተንበርክከው በሰው እና በንብረት ላይ ሊደርሱ የሚችሉትን አደጋዎች ያስቀሩበትን የአባቶች ተማጽኖ ተምሳሌታዊ ምስል እንዲሁም የኢትዮጵያ የሰላም እናቶችን ምስለ-ተማጽኖ ማየታቸውን፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አድንቀዋል፡፡
ተቋሙ በዘመናዊ አደረጃጀት ተልዕኮውን ለመፈጸም በሚያስችል ቁመና ላይ እንዳለ የተረዳ መሆኑን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው፤ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት የመከታተያ ዘዴ በቴክኖሎጂ መደገፉ ጥሩ ነው ብሏል፡፡
ነገር ግን ሕዝቡ በዚህ ዘዴ መንግሥትን እንዲያግዝ የሚያደርግ የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል፡፡
በተለያዩ የምክክር መድረኮች መፍትሔ ያመጡ እና ለሰላም ዋጋ የከፈሉ አካላትም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሊታወሱ እንደሚገባም ጥቆማ ሰጥቷል፡፡
በሚኒስቴሩ የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው፤ በተቋሙ አዲስ የተሰራው አደረጃጀት ዕውቀትን መሠረት ያደረገ እንደሆነ መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት መከላከል የሚያስችሉ ሥርዓቶችን ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በግጭት አፈታት ዙሪያ ከክልሎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት የምንሰራ ይሆናል ብለዋል፡፡