በሀረሪ ክልል ለሚዲያ ተቋማት እውቅና ተሰጠ

መስከረም 22/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል የተካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሚዲያ ተቋማት የክልሉ መንግስት እውቅና ሰጠ።

በእውቅና አሰጣጥ ስነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሔኖክ ሙሉነህ እንዳሉት በክልሉ መስከረም 20/2014 ዓ.ም የተካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ምርጫዎች በተለየ መልኩ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ ተጠናቋል።

ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተጨማሪ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ አካላት፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት እና  ህዝቡ  ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ነው ያሉት።

በተለይም የሚዲያ ተቋማት ምርጫውን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ከማድረስ ባለፈ ህዝቡ ድምፁን እንዲሰጥ በማነሳሳት ምርጫው የተሳካ እንዲሆን የላቀ ሚና ተጫውተዋል ሲሉም ተናግረዋል።

የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ያመሰገኑት ኃላፊው፣ በቀጣይ በክልሉ በሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ተግባራት እያከናወኑት ያለውን ተግባር እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

ከዚህ ባለፈም ሀገሪቱ በውጭና በሀገር ውስጥ ጫናዎች በበረታበት በአሁኑ ወቅት ያለምንም የጸጥታ ችግር ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ ማካሄዷ የህዝቡና የመንግስትን ጥንካሬ የሚያመላክት ነው ብለዋል።

“ይህንን ጥንካሬያችንን ይዘን በመቀጠል በሀገራችን ተላላኪ መንግስት ለመመስረት የሚያደርጉትን ጥረት በቅንጅትና በመተባበር ልናከሽፍ ይገባል” በማለትም ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይም ለምርጫው ስኬታማነት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሚዲያ ተቋማት የእውቅናና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ትላንት በተካሄደው የእውቅና አሰጣጥ መርሃግብር ላይ የተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው አካላት መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።