በሀረሪ ክልል ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ 60 አመራሮች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ሚያዝያ 1/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል ኃላፊነታቸውን በአግባብ ባልተወጡ 60 የወረዳ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከልም 22 አመራሮች ከኃላፊነት መነሳታቸው፣ 10 ከደረጃ ዝቅ እንደተደረጉና ቀሪዎቹ ላይ ከከፍተኛ እስከ ቀላል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ተገልጿል።
ፓርቲው የጀመረውን የማጥራት ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለፀው፡፡
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱጀባር መሀመድ እንደገለፁት በአመራሩ ላይ የተወሰደው እርምጃ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ያለመ ነው፡፡
በተለይም ፓርቲው ባካሄደው 1ኛ ጉባኤ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች እና ከሕዝቡ ጋር ባደረጋው ውይይት የተነሱ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ እርምጃ ተወስዷል፡፡
በነባሮቹ ላይ ቦታ ላይ የተተኩት አዳዲስ አመራሮችም ሕዝቡን በማወያየትና ለጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ ተጨባጭ የለውጥ ሥራ ማከናወን እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ጃፋር ሱፍያን በበኩላቸው አዳዲስ የተመደቡ አመራሮች ምደባ የተካሄደው የትምህርትና ሥራ ብቃትን ያማከለ እና ከጎሰኝነትና ከሙስና አመለካከትና ተግባር በፀዳ መልኩ መካሄዱን ገልጸዋል።
ለአዳዲስ አመራሮች የሥራ መመሪያ መስጠቱን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል።