በሀረሪ ክልል የበጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

መጋቢት 21/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ የበጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናከር እንደሚገባ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አይሻ መሀመድ ገለጹ።
ሚኒስትሯ በሀረሪ ክልል ኤረር ወረዳ በበጋ መስኖ ልማት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ገብኝተዋል፡፡
በዚህም በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡
ጥልቅ ውሃ ጉድጋዶችን በመቆፈርና የመስኖ ውሃን በመጠቀም የተለያዩ የምግብ ሰብሎችን ምርት የማምረት ተግባሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው ያመላከቱት፡፡
በክልሉ አርሶ አደሩ የምግብ ሰብልና ሌሎች ምርቶችን በስፋት ማምረት እንዲችል የውሃ ግድብ ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት እንዲሁም በቴክኖሎጂና በግብዓት መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የጉብኝቱ አላማ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመስኖ ውሃ ፕሮጀክቶችን ለማከናወንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሠ መስተዳደርና የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሚስራ አብደላ ናቸው፡፡
የውሃ ግድች መገንባት አርሶ አደሩን ከዝናብ ጠባቂነት በማላቀቅ በአመት 3 ጊዜ ምርቶችን እንዲያመርት ያስችላልም ብለዋል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ እስራኤልና ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያላቸው ትስስር ጠንካራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አምባሳደሩ እስራኤል በኢትዮጵያ ለሚገኙ ክልሎች በግብርናው ዘርፍ ያላትን ልምድ ለማካፈልና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚከናወኑ ተግባራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራች መሆኗን አብራርተዋል፡፡
እንደ ሀረሪ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ እስራኤል በቀጣይም እየተከናወኑ በሚገኙ የግብርና ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል፡፡