በሀረሪ ክልል የተገነባው አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክት ተመረቀ

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል የተገነባው አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክት (ላንድ ማርክ) በቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እና በሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተመርቆ ተከፍቷል።

በምረቃው መርሃግብር ላይም የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ እንዳሉት አብዛኞቹ ቅርሶችና የቱሪስት መስህቦች መረጃ የሚሰጡ አቅጣጫ ጠቋሚ የላቸውም።

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይህንን ችግር የሚቀርፉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

አቅጣጫ ጠቋሚዎቹም ባህላዊ እሴቶችን እና ታሪካዊ ይዘታቸውን በጠበቀ እንዲሁም የአካባቢው ቋንቋዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ተወለዳ አብዶሽ በቱሪዝም ሚኒስቴር ኢኒሼቲቭ የመዳረሻ ልማት በሀረር ከተማ መግቢያ ላይ የተገነባው ይህ ምልክት የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ከማጎልበት አንፃር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ከሚኒስቴሩ እና ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ክልሉን የሚጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጭ ጉብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

ሀረር ጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ መዳረሻ በሆነው ሀማሬሳ አካባቢ በተገነባው አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክት ምረቃ ላይም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሐረር ቅርንጫፍ)