በሀረሪ ክልል “የነጩ ፖስት ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” ንቅናቄ መጀመር

መስከረም 7/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል “የነጩ ፖስት ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” ንቅናቄ የማስጀመሪያ መርኃግብር በዛሬው እለት ተካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ዘመቻውን ባስጀመሩበት  ወቅት  ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በተለይም በአሁኑ ወቅት የአማራ እና አፋር ክልል ህዝቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ብለዋል።

በርካታ የዓለም መገናኛ ብዙሃንም ይህንን እውነታውን ወደ ጎን በመተው የተዛባ መረጃ እያቀረቡ ለማደናገር እየጣሩ ይገኛሉ፤ በመሆኑም “የነጩ ፖስት ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” ዘመቻ የኢትዮጵያን እውነተኛ መረጃ በመግለጽ የሽብርተኛውን ህወሓት ሃገር የማፍረስ ሴራ ለሌላው ዓለም ለማሳወቅ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ” የአሜሪካው ፕሬዚዳንትም የዘመቻውን መልዕክት ተቀብለው በመረዳት ተገቢውን ምላሽ ይሰጣሉ ብለን እናምናለን”  ማለታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ በበኩላቸው÷ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት የህወሓት የሽብር ቡድን ተግባራትን በቸልተኝነት ከመመልከት ለአሸባሪው ቡድን ያላቸውን ወገንተኝነት እየገለፁ ይገኛሉ ብለዋል።

“የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት”  ዘመቻም ምዕራባውያን ጉዳዩን እንዲያጤኑት እና እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጠቁመው ኢትዮጵያዊያንም የሽብር ቡድኑን እስከመጨረሻው ለማስወገድ እያደረጉ ያለውን ጥረት የሚያግዝ ስለመሆኑ አንስተዋል።