በሀገራችን የመጣውን አደጋ አብረን እንመክታለን – የትግራይ ተወላጆች

መስከረም 9/2014 (ዋልታ) የትግራይ ተወላጅ በሀገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተዋልዶና ተዛምዶ የሚኖር ህዝብ ነውና በሀገራችን የመጣውን አደጋ አብረን እንመክታለን ሲሉ የክልሉ ተወላጆች ተናገሩ።

በሀረሪ ክልል የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ጋር ተወያይተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙ የትግራይ ተወላጆች እንዳሉት አሸባሪው ህውሃት፣ አልሸባብና ኦነግ ሸኔን ለመከላከል ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት እንሰራለን ብለዋል።

እኛ የትግራይ ተወላጅ በሀገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተዋልዶና ተዛምዶ የሚኖር ህዝብ ነው፤ በሀገራችን የመጣውን አደጋ አብረን እንመክታለን ሲሉ ተናግረዋል።

የጥፋት ተልዕኮ ያላቸው አካላትን አጋልጠን በመስጠት ከመንግሥት ጎን በመቆም የአካባቢያችንን ሰላም እንጠብቃለንም ብለዋል።

ህፃናትን ማስተማር ሲገባ ለጦርነት መማገድ ወንጀል መሆኑን ጠቁመው መንግስትም እየወሰደ የሚገኘው ህግን የማስከበር እርምጃ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።

የአሸባሪው ህውሃት አመራሮች ልጆቻቸውን በውጭ ሀገራት እያስተማሩ የድሃውን ልጅ ለጦርነት እየማገደ ይገኛል ብለዋል።

እኛ ሰላም ነው የምንፈልገው፤ አሸባሪው ህውሃት እና የትግራይ ህዝብ የተለያዩ ናቸው ይህንን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ ሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አብዱልሃኪም ኡመር እንዳሉት አሸባሪው ህውሃት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ሀገርን ለማፍረስ እየሰራ ይገኛል።

መንግስት በተደጋጋሚ ለሰላም እጁን የዘረጋ ቢሆንም ህውሃት ግን በእምቢተኝነቱ ቀጥሏል ብለዋል።

በተለይም የትግራይን ወጣቶች እያስጨፈጨፈ ያለው የሽብር ቡድን የትግራይ ተወላጆች ሊታገሉት ይገባል ነው ያሉት።

መንግስት ሁልጊዜም ለሰላም የማያወላዳ አቋም እንዳለው ጠቁመው በመሆኑም መንግስት የዘረጋውን የሰላም አማራጮች እንዲቀበል ግፊት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የትግራይ ተወላጆች የአካባቢን ሰላም መጠበቅ እና ከሌሎች ወንድም እህቱ ጋር ያለውን አብሮነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይም በክልሉ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የትግራይ ተወላጆች ተሳትፈዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)