በሀገራዊ የሰላም ግንባታ ዙሪያ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው

ሰኔ 11/2013 (ዋልታ) – “በሀገራዊ የሰላም ግንባታ ላይ የደህንነት እና የፀጥታ አካላት ዕይታ” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ጦር ኮሌጅ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከደህንነት እና ከፀጥታ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

የመከላከያ ጦር ኮሌጅ ከሰላም ሚኒስቴርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መድረክ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያደታ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና የደህንነት እና ፀጥታ አካላት ተገኝተዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰላም ግንባታ ዙርያ በዲፕሎማሲ ዕይታ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች እና ዕድሎች ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ አቅርበዋል።

የጎረቤት ሀገራት የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የምዕራባውያን ጫና እና የተለያዩ አሸባሪ ቡድኖች እንቅስቃሴ በሀገር ሰላም ግንባታ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንዳላቸው አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

የመካከለኛ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ምስራቅ አፍሪካ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚያደርጉት ፉክክርም ለሰላም ግንባታው ፈተና መሆኑንም አንስተዋል።

ሀገራዊ አንድነት እና ብዝሀነትን አጣጥሞ አለማስኬድ ደግሞ ለሰላም ግንባታ የሀገር ውስጥ ፈተና መሆኑም ያነሱት አምባሳደሩ አንድነትን እና ልዩነትን አጣጥሞ ማስኬድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከሁሉም የውጭ ሀገራት ጋር መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነትን መፍጠር ለሰላም ግንባታ ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

የፓናል ውይይቱ የደህንነት እና የፀጥታ አካላት በሰላም ግንባታ ላይ የጋራ አቋም እንዲይዙ ለማስቻል የተዘጋጀ ነው ተብሏል።

(በትዕግስት ዘላለም)