በህዳሴ ግድብ እና በትግራይ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሩሲያ በያዘችው አቋም ኢትዮጵያ ደስተኛ ነች – አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ

ነሃሴ 18/2013(ዋልታ) – በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሩሲያ በያዘችው አቋም ኢትዮጵያ ደስተኛ መሆኗን በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ከሩሲያ የዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ በወቅታዊ የትግራይ ክልል፣ በህዳሴ ግድብ እና በኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አምባሳደር አለማየሁ የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መንግስት እየሰራቸው ያሉትን ስራዎች በየደረጃው ለሚገኙ የሩሲያ ፌዴሬሽን መሪዎች ማብራሪያ መስጠታቸውን እና ሩሲያም ጉዳዩ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ችግሩን በራሳቸው ይፈቱታል የሚል እምነት እና አቋም እንድትይዝ መደረጉን አንስተዋል፡፡

አምባሳደሩ አክለውም ሩሲያ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የውጭ ሀይሎች መሳተፍ ካለባቸው እንኳ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ሊያግዝ በሚችል መልኩ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንጂ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት በማውገዝ እና ሆን ብሎ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም ሽብርተኞችን ሊደግፍ በሚችል መልኩ መሆን እንደሌለበትም በአቋም ደረጃ መያዟ የሚያስመሰግናት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል-አቀባይ የሆኑት ማሪያ ዛኮሮቫ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ፣ አካባቢያዊ ተቋማት እና ራሳቸው ኢትዮጵያውያን መንግስት በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት እና ህዝቦች ወደ መደበኛ ኑሯቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ አለባቸው ማለታቸው ዘገባው አስታውሷል፡፡

በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይም ሩሲያ የያዘችው አቋም ኢትዮጵያን እንዳስደሰታት አምባሳደሩ ገልጸው ይህም ሶስቱ ሀገራት በመካከላቸው ያለውን ውዝግብ በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሰላማዊ መልኩ በድርድር መፍታት ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ እና ይህንን ማድረግ የሚችሉበት አቅም እንዳላቸውም እንደምታምን መግለጿን ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሩ አክለውም በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ያለውን ውዝግብ ሶስቱ ሀገራት በመልካም ግንኙነት ላይ በተመሰረተ የትብብር መንፈስ እና በድርድር መፍታት ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ኢትዮጵያ ታምናለች ብለዋል፡፡

አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ከዜና አውታሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያነሱት ሌላ ጉዳይ በሩሲያ የተመረተው ስፑትኒክ ቪ የተባለውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባትን የተመለከተ ሲሆን ኢትዮጵያ በቅርቡ ይህን ክትባት እንደምታገኝ ገልጸዋል፡፡

ይህን ክትባት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ማሳለፉን ያስታወቁት አምባሳደር አለማየሁ የቀሩትም የተወሰኑ ቴክኒካል ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡