በህገወጥ መንገድ የተከማቸ 800 ኩንታል ባቄላ በቁጥጥር ስር ዋለ

ነሃሴ 18/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በአንድ መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የተገኘ 800 ኩንታል ባቄላ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ።

በክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ተሾመ ጫካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ የግለሰብ መጋዘን ውስጥ የእህል ክምችት መኖሩን ከህብረተሰብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በመጋዘኑ ውስጥ በተደረገ ብርበራ 800 ኩንታል ባቄላ ተከማችቶ መገኘቱን ፖሊስ ገልጿል፡፡

እህሉን አከማችቷል የተባለውን ግለሰብም በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ ነው ፖሊስ የገለጸው፡፡

ህብረተሰቡ ለፖሊስ እያደረገ ያለው እገዛ ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የጠቀሰው ፖሊስ ፤ሕብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገር አፍራሽ የሆኑ ማናቸውንም ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን በማጋለጥ ትብብሩን አጠናክሮ ሊቀጥል እና አካባቢውን በንቃት ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስቧል።