በሆስፒታሉ ግንባታ መጓተት ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን የማሻ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

ሰኔ 25/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሸካ ዞን ማሻ ከተማ አስተዳደር እየተገነባ የሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ በመጓተቱ ለከፋ የጤና አገልግሎት ችግር መዳረጋቸውን የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሂደት በርካታ ወላጅ እናቶችና አስቸኳይ ህክምና የሚያፈልጋቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ለሞትና ለከፋ እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን ለዋልታ ቴሌቪዥን አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የሆስፒታሉ ግንባታ በፍጥነት ተጠናቆ በአቅራቢያቸው አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠርላቸውም አሳስበዋል፡፡

በሆስፒታል ደረጃ የጤና አገልግሎት ለማግኘት በአስቸጋሪ መንገድና መልከዓ-ምድር እስከ 80 ኪሎ ሜትር ድረስ ለመጓዝ ይገደዱ ለነበሩት የማሻ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የሆስፒታሉ ግንባታ መጀመር ትልቅ ደስታና ተስፋ የፈጠረ አጋጣሚ ነበር፡፡

የሆስፒታሉ ግንባታ በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም ሳይጠናቀቅ 6 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

በዚህ ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ህክምና ለማግኘት በአስቸጋሪ መንገድ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በዚህም በሆስፒታሉ ግንባታ መጀመር ተስፋ ያደረጉት የማሻ ከተማ ነዋሪዎች  ዛሬ ላይ ተስፋቸው ወደ ቅሬታ ተቀይሯል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምንም እንኳን ክልል ሆኖ ከተደራጀ አጭር ጊዜ ቢሆንም ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ምትኩ ታመነ የማሻ ሆስፒታልን ለማጠናቀቅ የግንባታ ውል የፈጸመውን ተቋራጭ ውል በማቋረጥ ክልሉ በራስ አቅም ግንባውን ለማጠናቀቅና በአጭር ጊዜ ሆስፒታሉን ሥራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ሆስፒታሉ በክልሉ ውስጥ ልዩ ትኩረት ከተሰጣው ግንባታዎች መካከል አንዱና ዋናው መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

የሆስፒታሉ ግንባታ ከተያዘለት ጊዜ የዘገየ በመሆኑ ግንባታውን ለማፋጠን ከተቋራጩ ጋር ያለውን ውል በማቋረጥ ክልሉ ቀሪ ሥራዎችን በራስ አቅም ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅትቶች ተደርገዋል ብለዋል፡፡

የሆስፒታሉን ግንባታ የተረከበው ተቋራጭም ቢሆን  ተቀማጭነቱን አዲስ አበባ አድርጎ በውስን ሰራተኞች ለሚንቀሳቀስ ሌላ አነስተኛ ተቋራጭ ሥራውን ከማስተላለፍ የዘለለ ግንባታውን በቅርብ የሚከታተል አካል አለመኖሩን የዋልታ ቴሌቪዥን የጋዜጠኞች ቡድን በስፍራው በመገኘት ታዝቧል፡፡

በነስረዲን ኑሩ