በሐረሪ ክልል አሻባሪዎቹን ሕወሓትና ሸኔን የሚያወግዝና ሰልፍ ተካሄደ

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) በሐረሪ ክልል አሻባሪዎቹን ሕወሓትና ሸኔን የሚያወግዝና የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላትን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሄደ።
በከሀዲዎች መቃብር ላይ የኢትዮጵያን ብልፅግና እናረጋግጣለን ሲሉም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አሸባሪው ሕወሓት ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን ሲጨቁንና ሲዘርፍ ቆይቷል፤ በአሁኑ ወቅት ወቅት ደግሞ አገር የማፍረስ ሙከራ ላይ ነው ግን አይሳካለትም ብለዋል።
የክልሉ ነዋሪዎች አሸባሪዎቹን ሕወሓትና ሸኔን በመቃወም ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጎን መሆናቸውን በታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ ገልፀዋል።
የክልሉ የከተማ እና የገጠር ነዋሪዎች፣ ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ የመንግስት ሠራተኞች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሐረር ከተማ ዋና ዋና አደባባዮች አሸባሪና አገር አፍራሾቹን ሕወሓትና ሸኔን ሲያወግዙ አርፍደዋል።
ሰልፈኞቹ ‘ጁንታው የኢትዮጵያ ጠላት ነው፣ ሃላፊነታችን ታሪካዊ ነው!፣ ለወራሪ ጠላት አንበረከክም፣ እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ ለውጫዊ ጫና የሚንበረከክ ማንነት የለንም!!፣ ኢትዮጵያ በውክልና ጦርነት አትንበረከክም!’ የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።
ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመቆምና በግንባር በመሠለፍ አገርን ለማዳን እንደሚዘምቱም ሰልፈኞቹ በያዟቸው መፈክሮች ገልፀዋል።