በመሪዋ የተበረታታችው ጫማ አስዋቢ (ሊስትሮ)

መኖሪዋን አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ ያደረገችው አረጋሽ አንጄቶ ማልዳ ተነስታ ልጆቿን ትምህርት ቤት አድርሳ የዕለት እንጀራዋ ወደሆነው የጫማ ማስዋብ (ሊስትሮ) ስራዋ ታመራለች፡፡

ታዲያ አረጋሽ ላለፉት ሰባት ዓመታት ብዙ ችግሮችን እየተጋፈጠች ብዙን ጊዜ የወንዶች ስራ ተብሎ የሚታሰበውንና ጥቂት ሴቶች የሚደፍሩትን የሊስትሮ ስራ እየሰራች ህይወቷን ትመራለች።

ይህንንም ስሜት ለአዲስ ዋልታ ባጋራችበት ወቅት እኔ ያለፍኩበት የችግር መንገድ ልጆቼ እንዳይቀምሱት ዘውትር እታትራለሁኝ የምትለዋ አረጋሽ አንጄቶ ህልሟ ጠንክሮ በመስራት ውስጥ ችግርን ተጋፍጦ ማለፍን የሰነቀ መሆኑን ታስመሰክራለች፡፡

ታዲያ በዚህ ስራዋ ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የምታገለግለዋ ብርቱዋ አረጋሽ ባልጠበቀችው ሁኔታ ሰሞኑን የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑትን ዐቢይ አሕመድን ጫማ የማስዋብ እድል በማግኘቷ የተሰማትን ስሜት ስትገልጽ “ድንገታዊ ድንጋጤ ወሮኛል’’ ስትል በአግራሞት ሁኔታውን ታስታውሳለች፡፡

በእርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሥራ ቦታዬ ከመገኘታቸው አልፈውም እኔን በማበረታታቸው ብቻ ዛሬ ላይ የሥራ ሞራሌ ትልቅ ሆኗል ስትልም ትናገራናለች፡፡

በሊስትሮ ሥራዋ ከሰባት ዓመታት በላይ ቦታዎችን እየቀያየረች ሳትሰለች እና ሥራዋን ሳትንቅ የምትሰራው አረጋሽ አንጄቶ ለእኔ የሊስትሮ ሥራዬ ወርቅ እና ጌጤ ነው ስትልም በመናገር በሥራዬ ሁል ጊዜ የሚያበረታቱኝን ሁሉ አመሰግናለሁ ስትልም መልዕክቷን አስተላልፋለች።

በግዛቸው ይገረሙ