በመሬት ውስጥ የሚገነባውን የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ተባለ

ጥቅምት 14/2015 (ዋልታ) በመሬት ውስጥ የሚሰራው የየካ ቁጥር ሁለት የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክት የነበሩበትን ችግሮች በመቅረፍ ግንባታውን ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

ከከተማው አስተዳደር ግዙፍ የልማት ግንባታዎች መካከል፤ ይህ ሾላ ገበያ አካባቢ በመሬት ውስጥ እየተገነባ የሚገኘው የየካ ቁጥር ሁለት የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን የጠቀሰው አስተዳደሩ፣ ፕሮጀክቱ የነበሩበትን ችግሮች በመቅረፍ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በአስተዳደሩ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ደቦ ቱንካ ገልጸዋል፡፡

በ 7 ሺሕ 247 ካሬ ላይ ይህ የመኪና ማቆሚያ ግንባታው ሲጠናቀቅ፤ ከዘጠኝ መቶ መኪኖች በላይ የመኪና ማቆሚያ ቦታ በማቅረብ፤ በአካባቢው ያለውን የመኪና ማቆሚያ ቦታ እጥረት በመቅረፍ፤ የአካባቢውን የትራፊክ ፍሰት እንደሚያሳልጥም ተመልክቷል።

የትራፊክ ፍሰት ችግርን ለመቅረፍና የተሽከርካሪ ደህንነትን ለመጠበቅ፤ ቀደም ሲል በሜጋ ፕሮጀክቶች የተገነቡትን ጨምሮ አሁንም በመገንባት ላይ ያሉት የመኪና ማቆሚያ ግንባታ ስራዎች፣ ለከተማዋ የትራፊክ ፍሰት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው አስተዳደሩ ማስታወቁን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡