በመቄዶንያ ማዕከል ውስጥ ለሚገኙ 200 አረጋዊያን የኮቪድ-19 ክትባት ተሰጠ

ሚያዝያ 06/2013 (ዋልታ) – በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ማዕከል ውስጥ ለሚገኙ 200 አረጋዊያን የኮቪድ-19 ክትባት ተሰጥቷል፡፡

በዛሬው ዕለት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ውስጥ ለተረጂዎች በመጀመሪያ ዙር ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው 200 አረጋዊያን ክትባቱ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በቀጣይ ቀናቶችም ለሁሉም ተረጂዎች ክትባት የሚሰጡ መሆኑን ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማሕበር በአሁኑ ሰዓት 4 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ራሳቸውን ችለው መንቀሰሳቀስ፣ መመገብ እና መፀዳዳት የማይችሉ አረጋውያንንና አዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳናዎች ላይ በማንሳት የመጠለያ፣ የምግብ፣ የልብስ፣ የሕክምና አገልግሎትና ቤተሰባዊ ፍቅር በመስጠት ደጋፊና ጧሪ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንን እየረዳ ይገኛል፡፡

ማእከሉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በአማራና ትግራይ ክልሎች ቦታ በመረከብ ረዳት የሌላቸውን አቅመ ደካሞች በመመገብና በመንከባከብ ላይ የሚገኝ ተቋም ነው።