በመተከል ዞን ችግር የተፈጠረው ጁንታው የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ከጥፋት ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ በመንቀሳቀሱ ነው – ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ

የካቲት 30/2013 (ዋልታ) – በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ችግር የተፈጠረው ጁንታው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ከጥፋት ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ በመንቀሳቀሱ እንደነበር የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ተናገሩ።

በዞኑ የጉባ ወረዳ ነዋሪዎች በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

በዞኑ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል ከነዋሪዎቹ ጋር የተወያየ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሚናቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ግብረ ኃይሉ በዞኑ ከተቋቋመ ወዲህ የወረዳው ሰላምና ፀጥታ መሻሻል እንደታየበት መስክረዋል።
ከግብረ ኃይሉ ጋር በመቀናጀትም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንደሚተጉ ተናግረዋል።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ መንግሥት የአካባቢውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ተናግረው፣ ወደ ልማት ለመግባትም ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።

በአካባቢው ችግር የተፈጠረው ጁንታው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ከጥፋት ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ በመንቀሳቀሱ እንደነበር አስረድተዋል።

ህብረተሰቡም አንድነቱን በማጠናከር ሰላምን ማረጋገጥና ለልማት መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ግብረ ኃይሉ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እስኪረጋገጥ ጥረቱን እንደማያቋርጥ ሌተናል ጄኔራል አስራት አረጋግጠዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባበሪ አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አንድነቱን እንዲያጠናከር ማሳሰባቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

“አንድነታችንን የምናረጋግጥ ከሆነ ሰላማችንን የሚያደፈርስ አካል አይኖርም” ብለዋል።