በመዲናዋ በህገወጥ መንገድ የተዘረጋ የኤሌክትሪክ መስመርና ቆጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

የኤሌክትሪክ መስመርና ቆጣሪ

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ በህገወጥ መንገድ የተዘረጋ የኤሌክትሪክ መስመርና ቆጣሪ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ አስታውቋል፡፡

በአገልግሎቱ የምስራቅ አዲስ አበባ ዲስትሪክት ቁጥር 5 አገልግሎት መስጫ ማዕከል እንዳስታወቀው ከኅብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ መሰረት ከአካባቢው ፖሊስ ጋር በመተባበር በተደረገ አሰሳ ስምንት ምሰሶ ተተክሎ፣ መስመር ተዘርግቶ 12 ቆጣሪ በህገ-ወጥ መንገድ ተገጥመው አገልግሎት ሲሰጡ ተገኝቷል፡፡

ልዩ ስሙ ወጂ መድኃኒዓለም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ የኤሌክትሪክ መስመሮች ዘርግተው የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ሲጠቀሙ እንደተገኙ ማዕከሉ አስታውቋል፡፡

በከተማው በህገ-ወጥ መንገድ የተዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመሮችን የማፍረስና የተገጠሙ ቆጣሪዎችን የማንሳት እርምጃ መወሰዱም ተመልክቷል፡፡

የተገጠሙ ቆጣሪዎች ተቋሙ የማያውቃቸው እና የተቋሙ አርማ የሌላቸው መሆናቸው በእርምጃው ወቅት መረጋገጡንም ጠቁሟል፡፡

ደንበኞች አዲስ ቆጣሪ ማስገባት ሲፈልጉ ተቋሙ ያስቀመጠው የአሰራር ሥርዓት መሰረት እና ህጋዊ መንገድን በተከተለ መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡

ኅብረተሰቡም መሰል እኩይ ተግባር ሲመለከት ለተቋሙና ለህግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥና ህገ ወጥ ተግባርን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ማሳሰቡን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW