በመዲናዋ ከሁሉም ክፍለ ከተማ የተወጣጡ ሴቶች ችግኝ ተከሉ

ሐምሌ 02/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ ከሁሉም ክፍለ ከተማ የተወጣጡ 10ሺህ የሚሆኑ ሴቶች በለሚኩራ ዕጽዋት ማዕከል በመገኘት ከ20 ሺህ በላይ ችግኞችን ተክለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴን ጨምሮ የብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ኃላፊ መስከረም አበበ በለሚኩራ የዕጽዋት ማዕከል በመገኘት አረንጓዴ አሻራቸውን አስቀምጠዋል፡፡
አፈ ጉባኤ ዘርፈሽዋል ንጉሴ እንደገለጹት የሴቶች ችግኝ መትከል ልክ እንደ ህፃናት ከፍተኛ ትኩረትና እንክብካቤ ከማድረግ አኳያ መልካም ትውልድ እና ሀገርን ለመገንባት ወሳኝነት አለው ብለዋል።
ዛሬ የተተከሉ ችግኞችም ለነገይቱ ኢትዮጵያ እና አዲስ አበባ ልምላሜ የተላበሰች፣ ለኑሮ የተመቸች እንድትሆን የሚያደርግ በመሆኑ ሴቶች ልክ እንደ ልጆቻቸው የተከሏቸውን ችግኞች ለመንከባከብ ቃል ገብተዋል ሲሉም አክለዋል፡፡
መትከል ብቻ ሳይሆን መኮትኮት እና መንከባከብ ይገባል ሲሉ አፈ ጉባኤዋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ አስጀማሪነት በወርሃ ክረምት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በመከተል ሁሉም ማህበረሰብ በነቂስ በመሳተፍ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ ይገባል ሲሉም የለሜ ኩራ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚ ኤልያስ መሀመድ ገልጸዋል፡፡
ሴቶች የተከሉትን ችግኝ ፍሬ እንዲያፈራ ልክ እንደ ልጆቻቸው መንከባከብ እና መጠበቅ አለባቸው ሲሉም አቶ ኤልያስ አክለዋል፡፡
(በአመለወርቅ መኳንንት)