በመዲናዋ የሚከናወን ህገወጥ እርድ ለህብረተሰቡ ከፍተኛ የጤና ስጋት መሆኑን የቄራዎች ድርጅት ገለጸ

የቄራዎች ድርጅት

ሚያዝያ 20/2013 (ዋልታ) – በመዲናዋ የሚከናወን ህገወጥ እርድ ለህብረተሰቡ ከፍተኛ የጤና ስጋት መሆኑን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ገለጸ።

ህገወጥ እርዱ ከጤና ስጋትነቱ በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩን በየዓመቱ በአማካይ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ እያሳጣው መሆኑም ተገልጿል።

ድርጅቱ ለትንሳኤ በዓል ጤናማነቱ የተረጋገጠ የእንስሳት እርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጉንም አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ከከተማ አስተዳደሩ አርሶአደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ጋር በመሆን በዓሉን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶአደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፍቅርተ ነጋሽ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ህገወጥ እርድ እንደሚፈጸም ገልጸው፣ እርዶቹ በወንዞች አካባቢ፣ በሆቴሎች ጀርባና በተለያዩ ቆሻሻ ቦታዎች ስለሚከናወን ለጤና ስጋት ነው ብለዋል።

ከእንስሳት ወደ ሰው ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች ከማጋለጥ በተጨመሪ ሥጋው ስለሚመረዝ የጤና ስጋትነቱ የጎላ እንደሆነና አሁን እየተስፋፋ ከመጣው የኮቪድ ስርጭትም አንፃር ጉዳቱ የከፋ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ህገ ወጥ እርድ በሚያከናውኑ አካላት ላይ ከ15 ሺህ እስከ 25 ሺህ ብር ቅጣትና ከሁለት እስከ ሦስት ወር የእስር ቅጣት ማስቀመጡንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ በየትኛውም ቦታ ህገወጥ እርድን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በበኩሉ፣ ለመጭው የትንሳኤ በዓል ጤናማነቱ የተረጋገጠ የእንስሳት እርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማደረጉን አስታውቋል።

የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረሚካኤል ለመጭው የንትሳኤ በዓል በድርጅቱ ከ4ሺህ 500 እስከ 5ሺህ የሰንጋ፣ የበግና የፍየል እርድ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።

የሥጋ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን የማደስና ዝግጁ የማድረግ፣ የቁም እንሳሰቱ ማደሪያና የእርድ ቦታን የማስተካከል ሥራ መሰራቱን ተናግርዋል።

በእርድ አገልግሎቱ ሉካንዳ ቤቶች ከሚያሳርዱት በተጨማሪ ለከተማዋ ነዋሪ የበሬ፣ ፍየልና በግ እንስሳት እርድ አገልግሎት እንደሚሰጥም አመልክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በእርድ አገልግሎቱ ለበሬ 800 ብር፣ ለበግና ፍየል እያንዳንዳቸው 100 ብር ብቻ እንደሚያስከፍል ገልጸዋል።

የእርድ አገልግሎቱ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያስችል መልኩ እንደሚከናወንም አረጋግጠዋል።